አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ ከሚል አመለካከት በመውጣት ለሀገር የሚሰጡትን ጥቅም በሚያሳይ አስተሳሰብ ወደፊት መጓዝ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ29ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረው አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በባህርዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀምሯል

አካል ጉዳተኞችን አካታች፣ ምቹና ዘላቂ የተሻለ ዓለምን በድህረ ኮቪድ-19 እንገንባ!›› በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ በባህርዳር ከተማ ታህሳስ 17 እና 18 ቀን 2013 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የሚከበረው 28ኛው አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በተለያዩ ፕሮግራሞች በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በእለቱ መርሀ ግብር የአካል ጉዳተኞች ስፖርታዊ ውድድር፣ የኪነጥበብ ስራዎች እንዲሁም የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን የአካል ጉዳተኞች አካቶ መርሀ ግብር እና የበአሉ መሪ ቃል በተመለከተ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎል፡፡

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በውይይት መድረኩ የአካል ጉዳት አይነቱ ብዙ እንደመሆኑ የሚሰጡ ምላሻችም በዛው ልክ ብዙ መሆናቸውን ገልፀው ያሉ ችግሮች እንደሚፈቱ በማሰብ በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞችን እንዲጠቀሙ ከሚል አመለካከት በመውጣት ለሀገር የሚሰጡትን ጥቅም በሚያሳይ አስተሳሰብ ወደፊት መጓዝ እንደሚገባ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከላይ ጀምሮ በየመዋቅሩ ያሉ የመንግስት አካላት ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

የአካል ጉዳተኞች ጥያቄ በሀብት ውስንነት ብቻ ሳይሆን የግንዛቤ ችግር በመሆኑ የህግ ማዕቀፎች ተፈፃሚነት ላይ ክፍተት ፈጥሯል ያሉት የአማራ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ አካል ጉተኞችን የልማቱ ተሳታፊ በማድረግ ከአበርክቶዋቸውን ሀገር እንድትጠቀም ለማድረግ አመለካከት ላይ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ምህረት ንጉሴ በበኩላቸው ማህበሩ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር እንደሚሰራ ገልፀው አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ስምምነቶችና የህግ ማእቀፎች እንዲፈፀሙ አስገዳጅ ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእለቱ ፕሮግራም በጧፍ ማብራትና በፖሊስ ማርሽ ባንድ በታጀበ የእግር ጉዞ ተጠናቋል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Font size
Colors