የተረጂነት አመለካከት እየተወገደ በማብቃትና በማሳተፍ ዘላቂ ጎዳና በመጓዝ የአካል ጉዳተኞችን እምቅ አቅም ለልማት መጠቀም ይገባል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ29ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረው አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን “አካል ጉዳተኞችን አካታች፣ ምቹና ዘላቂ የተሻለ ዓለምን በድህረ ኮቪድ-19 እንገንባ!›› በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ በባህርዳር ከተማ ለሁለት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል ፡፡

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር የተረጂነት አመለካከት እየተወገደ በማብቃትና በማሳተፍ ዘላቂ ጎዳና በመጓዝ አካታችነትና እኩልነት የተረጋገጠበት ማህበራዊ ድባብ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡፡

መሪ ቃሉ የያዘው ለአካል ጉዳተኞችን ምቹ፣ አካታችና ዘላቂ ዓለምን የመገንባት መልእክት የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት ሰብሮ በመውጣት የአካል ጉዳተኞችን አቅም ለልማት መጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ለአካል ጉዳተኞች መብት ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገ ሲሆን ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ፣ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መብትና ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን አዋጅ፣ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች የድርጊት መርሃ ግብርና የአካላዊ ተሐድሶ ስትራቴጂ፣ ለአካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ የማስገባት መመርያ ወጥቶ እየተሰራ ሲሆን በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያግዝ ‹‹የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ›› በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

አካል ጉዳተኞችን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትኩረት የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት በጋራ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው በክልሉ ካሉ አካል ጉዳተኞች አንፃር የሚሰጠው አገልግሎት የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ገልፀው ለአካል ጉዳተኞች መስራት ችሮታ ሳይሆን ህገመንግስታዊ መብታቸውን ማክበርና ማስከበር በመሆኑ መንግታዊ ሀላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን አካል ጉዳተኞችን ለማስተዋወቅ፣ አካታች ማህበረሰብ ለመፍጠር፣ ግንዛቤ ለማስረፅ አልሞ በየአመቱ እንደሚከበር የተናገሩት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ምህረት ንጉሴ በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ሃያ ሚሊዮን የሚሆኑትን አካል ጉዳተኞች በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት፣ በስራ እድል፣ በመረጃ ተደራሽነት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወደኃላ እንዳይቀሩ ሁሉም ተገቢ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በበዓሉ ስፖርታዊ ውድድር የፓናል ውይይት፣ ኤግዝቢሽን ፣ የእግር ጉዞ ፣ የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን በፓናል ውይይቱ ተሳተፊዎች የአካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ ከአመለካከት ጀምሮ እስከ ተሳትፎ ለውጦች መኖራቸውን ጠቁመው ዘላቂነት ያለው ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ተጠቃሚነት እዲመጣ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በአካል ጉዳተኞች ላይ ለሰሩና በጎ አስተዋፆ ላበረከቱ እንዲሁም ለበአሉ መሳካት የበኩላቸውን ላደረጉ የምስጋናና የእውቅና ሰርተፍኬት እና ስጦታ ተበርክቷል::

ቀጣዩ አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በጂግጂጋ እንደሚከበር ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Font size
Colors