አስከፊ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስና ጨርሶ ለማስወገድ በጋራና በተናጥል ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ተባለ።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሶስተኛው ዙር አስከፊ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መከላከያና ማስወገጃ ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር የማስጀመሪያ ፕሮግራም ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሂዷል።
ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ በሀገራችን ለ13ኛ ጊዜ “ህፃናትን ከጉልበት ብዝበዛ ለመታደግ አሁኑኑ የተግባር እርምጃ እንውሰድ!” በሚል መሪ ቃል የተከበረውን የአለም የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መከላከያና ማስወገጃ ቀንን አስመልክቶም መግለጫ ተሰጥቷል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ከ2013 እስከ 2017ዓ.ም ለመተግበር የተዘጋጀውን አስከፊ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መከላከያና ማስወገጃ ብሔራዊ የድርጊት መርሀግብር ተግባራዊ በማድረግ አስከፊ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስና ጨርሶ ለማስወገድ በጋራና በተናጥል ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ ተፈፃሚ ከሚያደርጋቸው ስትራቴጂክ ተግባራት መካከል ህፃናት ለአደጋና ለጉልበት ብዝበዛ በሚዳርጉ እና የመማር ሁኔታን በሚገድቡ የሥራ ዘርፎች ላይ እንዳይሰማሩ በጥናት ላይ የተመሰረተ የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የድጋፍ ሥራዎችን ማከናወን አንዱ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን በመከላከልና በማስወገድ ረገድ ባለፉት 10 ዓመታት በሁለት ዙር በባለድርሻ አካላት የጋራ ቅንጅት የተተገበሩት ሁለት የድርጊት መርሀ ግብሮች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል
ከ2013 – 2017 ዓ.ም ለመተግበር የተዘጋጀው የድርጊት መርሀ ግብር መከላከል፣ የህግ ጥበቃ መስጠትና መልሶ የማቋቋም ተግባርን የተመለከቱ ሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎችን መሠረት አድርጎ መዘጋጀቱን የተናገሩት ወ/ሮ አየለች ይህንን ማህበራዊ ችግር ለመከላከልና ደረጃ በደረጃ ለመቀነስ በስትራቴጂው በተቀመጠው መሰረት በጋራና በቅንጅት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ታደለ ይመር እድሜያቸው ለስራ ያልደረሱ ህፃናትን ወደ ትምህርት መላክ የሁሉም የቤት ሥራ መሆኑን ጠቁመው የድርጊት መርሀ ግብሩን በመተግበር ረገድ የተሰጠውን ድርሻ ለመወጣት ኮንፌዴሬሽኑ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ በጋራ ልንገታውና ልናስወግደው ይገባል ያሉት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍስሀፂሆን ቢያድግልኝ ፌዴሬሽኑ የድርጊት መርሀግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ የበኩሉን መወጣቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመድረኩ አስከፊ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን የመከላከልና የማስወገድ ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር እና የአለም የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መከላከያና ማስወገጃ ቀን መሪ ቃል የተመለከተ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Font size
Colors