ብሔራዊ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርአት ግንባታ በኢትዮጵያ ይፋ ተደረገ

ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ፡ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የሥራ ገበያ መረጃ ስርአትን ዲጂታላይዝድ ማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርአት ግንባታ በኢትዮጵያ ይፋ ተደርጓል፡፡


በይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኘተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት የብሄራዊ የሥራ መረጃ ስርዓት ግንባታ ያቀድነውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስርአት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገሩ በተጨማሪ ዜጎች በተለይም ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል የሥራ ገበያ መረጃን በተሻለ ፍጥነትና በበቂ መጠን እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል፡፡


በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው መልእክታቸውን ያስተላለፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አህመዲን መሀመድ በበኩላቸው የሥራ ገበያ መረጃን በሀገር ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው በጋራ እየተገበሩ መሆናቸውንና ተቋማቸው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡


የአለም ስራ ድርጅት ተወካይ ወ/ሮ አይዳ አወል በበኩላቸው የሥራ ገበያ መረጃ በሀገር ደረጃ መተገበሩ አስፈላጊ መሆኑንና ድርጅታቸው የብሔራዊ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርአት ግንባታን በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ የአፍሪካ ህብረት ተወካይ የሆኑት ኦማር ዲዮፕ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓትን መዘርጋት ለኢትዮጵያ አሰፈላጊና ወቅታዊ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን በተለይም ይህንን ዓላማ ስኬታማ ለማድረግ ከአፍሪካ ከተመረጡ ጥቂት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ሀገሪቷ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰጠችውን ሰፊ ትኩረትና ዝግጁነት ያመላክታል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Font size
Colors