ውሎ አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ወደ ማእከል የማስገባት ስነ- ስርአት ተከናወነ

ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም ሐዋሳ፡ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሐዋሳ ከተማ የሚገኙ 12ዐ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው ውሎ አዳራቸውን በጐዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ድጋፍ ወደ ሚያገኙበት ማዕከል የማስገባት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡
በእለቱ የሜሪ ጆይ የወጣቶችና ህጻናት ማእከልን በመጎብኝት መልእክት ያስተላለፉት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት መንግስት ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያንን ለማቋቋም በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኘና ከተለያዩ የግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የድጋፍ ስራው ስኬታማ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት አያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
የማእከሉ መስራችና የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ዋና ሃላፊ የሆኑት ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከ1994 ጀምሮ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካማ አረጋዊያንንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን የተለያዩ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝና በእለቱም የተከናወነው 120 ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውና ውሎ አዳራቸውን በጐዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ለድጋፍና እንክብካቤ ወደ ማዕከል የማስገባት ሥነስርዓት የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በሬሶ እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ደጋፊ የሌላቸውና ውሎ አዳራቸውን በጐዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ለመደገፍ በድርጅቱ በኩል ለተከናወኑ የበጎ አድራጎት ስራዎች ምስጋናቸውን በማቅረብ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Font size
Colors