የመተጋገዝና የመረዳዳት እሴቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

ሐምሌ 10 ቀን 2013 .ምአዲስአበባ፡የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የክረምት በጎ አድራጎት ሥራና የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በማስፋት በኦሮሚያ  ክልል በአርሲ ዞን ጮሌ ወረዳ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን አመራሮች፣ የግል ድርጅቶችና ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ  አመራሮችና ሰራተኞች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች  እንዲሁም የወረዳው አመራሮችና ነዋሪዎች በተገኙበት የችግኝ ተከላ ፕሮግራምና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቤት የማደስ መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡

የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የተከናወነው በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ስም በተሰየመው ፓርክ እና በጮሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን የወረዳው ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የበጎ አድራጎት ክበብ አባላት ተሳትፈዋል፡፡ በተመሳሳይ በእለቱ የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቤት የማደስ ፕሮግራም በይፋ ተጀምሯል፡፡

በእለቱ  የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የወረዳው አስተዳደር ሃላፊ አቶ ቃኘው ዳኘው  በከፍተኛ መንግስት የሥራ ሃላፊዎች በኩል በወረዳው  ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርና የገቢ ምንጫቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቤት የማደስ ፕሮግራም  ለወረዳው ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር ተግባር ነው ብለዋል፡፡ 

ፕሮግራሙን በማስመልከት መልእክት ያስተላለፉት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው  የወረዳው ነዋሪዎችንና አመራሮች በመተጋገዝ በኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መርዳት እንደሚገባና ሰውን ማእከል ያደረገ ተግባር ከተከናወነ በተለይም በጋራ ርብርብ የወረዳውን ወጣት ሃይል አምራች ዜጋ እንዲሆን ማድረግ ከተቻለ ችግሮቻችንን በቀላሉ መሻገር እንደሚቻል  ገልጸዋል፡፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቤት ለማደስ የሚውል አራት መቶ ሺህ ብር፣ በቀጣይ ለሚከበሩ በአላት የሚሆን ስልሳ ሺህ ብር ለሃይማኖት አባቶች ተወካዮች የተበረከተ ሲሆን እንዲሁም  ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግል ዊልቼርና ለግሷል፡፡ በመጨረሻም በወረዳው የመሰረተ ልማት ችግሮች ዙሪያ ነዋሪዎችንና የወረዳው አመራሮችን ያሳተፈ  ውይይት ተደርጓል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Font size
Colors